ክርስትና ሃይማኖት ወይስ ግንኙነት?

By Super Admin

ክርስትና ሃይማኖት ወይስ ግንኙነት?

በዘመናዊው የወንጌላዊያን እንቅስቃሴ በጣም በተደጋጋሚ የምንሰማው ሃሳብ፡ "ክርስቶስ ግንኙነት እንጂ ሃይማኖት ሊመሰርት አልመጣም" የሚል ነው። ይህ ሃሳብ እንዲሁ ስንሰማው ልከኛ የሚመስል ሃሳብ አለው። ብዙ ጊዜ ይህን ሃሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎች ማንሳት የፈለጉት ነጥብ ምን የሚል ነው፣ ዝምብሎ ከውጪ ቤተክርስትያን ስለተኬደ ብቻ፣ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ስላደረጉ ብቻ፣ ከክርስቶስ ጋር ግንኙነት ከሌለን ይሄ እምነት አያድንም፣ የክርስትና ዋነኛ ግብ ከክርስቶስ ጋር ህብረት ማረግ ነው እንጂ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እና ድርጊቶች ላይ ዝምብሎ መሳተፍ አይደለም የሚል ነው። መቼስ ይህን ሃሳብ የሚቃወም ይኖራል እንዴ? ሰው ዝምብሎ ከቅድስት ሥላሴ ጋር እውነተኛ በእምነት የተመሠረተ ግንኙነት ሳይኖረው፣ ዳግም ተወልዶ በመልካም ስራው ክርስቶስን የሚገልጥ ህይወት ሳይኖር ዝምብሎ ቤተክርስትያን ስለሄደ፣ የተለያዪ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ስለፈፅመ ብቻ ይድናል የሚል አይኖር? ለዚያ ይህ ሃሳብ ልክ ነው ማለት እንችል ይሆን?

ሉተራዊ ትችት

በመጀመሪያ ከላይ ከተነሳው ሃሳብ ጋር በከፊል ቢሆንም ሁሉም ክርስትያን ይስማማል፣ እኛ ሉተራዊያንም ቢሆን እንስማማለን። ሰው በእምነት ብቻ እንደሚድን በማመናችን፣ ሰው እውነተኛ እምነት ሳይኖረው፣ ማለትም በጌታ ላይ የተደገፈ፣ ፍሬን የማያፈራ እምነት ያድናል ብለን አናምንም። ዝምብሎ ቤተክርስትያን ስለተኬደና ሃይማንቶአዊ ስርዓቶች ላይ ስለተሳተፈ ብቻ ሰው ይድናል ብለን አናምንም። ለዚያ በዚህ መልኩ ከላይ ከተጠቀሰው ሃሳብ ጋር እንስማማ ይሆናል፣ ነገር ግን "ክርስትና ሃይማኖት ሳይሆን ግንኙነት ነው" የሚለው ፈጽሞ የተሳሳተ እና ከመጽሃፍ ቅዱስ የራቀ አባባል እንደሆነ እናምናለን። ትችቶቻችንን ከስር እናስቀምጣለን።

ሃይማኖት መጥፎ ቃል አይደለም

የመጀመሪያው አሳዛኝ ነገር እነዚህ ሰዎች ይህን ሃሳብ ለመግለጽ ሲፈልጉ ሃይማኖትን ከፈሪሳዊነት ጋር ወይም ከሙት እምነት ጋር በማቆራኘት፣ ለነዚህ ሰዎች ሃይማኖት ማለት ሙት እምነት መያዝ ከማለት ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን። ይሄ ፍጹም ፍጹም አሳዛኝ፣ አጸያፊም ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በመጽሃፍ ቅዱሳችን ጭምር ያለን ቃል ትርጉም ለውጦ ማጠልሸት ምንኛ የተሳሳተ መንገድ ነው። ከመጽሃፍ ቅዱስ በኋላም በዘማናት ሁሉ፣ በክርስትና 2000 አመት ታሪክ ሁሉም ክርስትያን በሚባል ደረጃ ሃይማኖትን(ማለትም እውነተኛውን ሃይማኖት) በአዎንታዊ እንጂ አሉታዊ መንገድ የሚረዳ ትውልድ ኖሮ አያቅም። ብዙ ብዙ ሰማዕታት ለሃይማኖቴ እሞታለው የሚሉት ቃላት የመጨረሻዎቹ ቃላቶቻቸው ሆነው በታሪክ መዛግብት እናገኛለን። ከዚያም አልፎ እነዚህ ሰዎች ለሃይማኖት የሰጡት ትርጓሜ ፍጹም ከመዝገበ ቃላት ወይም ከቋንቋ የመነጨ አይደለም፣ አንድን ሃሳብ ለመግለጽ በማሰብ ብቻ ሃሳባቸውን ለማጉላት ይህንን በክርስትያኖች የተወደደውን ቃል፣ በመስሃፍ ቅዱስ የተጠቀሰውን ቃል አጠለሹት። ይሄ ደሞ በጣም የቅርብ ጊዜ ታሪክም ነው፣ ምክንያቱም ደሬጄ እንኳን፡ "የጥንቱን ሃይማኖት ስጠኝ" የሚል የተወደደ መዝሙር ዘምሮ፣ ቃሉን በአሉታዊ መንገድ ማንም እንዳልወሰደው እንመለከታለን። እስቲ የቃሉን ትርጓሜ እናም የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶች አይተን ወደ ቀጣዪቹ ትችቶች እናልፋለን።

በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።'

ያዕቆብ 1:27

ቃሉ ደሞ የመጣው ከላቲኑ ስም "religio" የሚል ነው ይሄ ደሞ የመጣው ከነዚህ ሁለት ግሶች እንደሆነ የቋንቋ ምሁራን ይናገራሉ፡

  • Religare ይህም አጥብቆ ማሰር የሚል ፍቺ ያለው ቃል ነው። ይሄ የሚጠቁመው ሃይማኖት ሰዎችን ከአምላክ ጋር ያስራል የሚል ትርጉም አለው።

  • Relegere ይህም አብሮ መሰብሰብ የሚል ትርጉም አለው። ይሄ ደሞ የሚጠቁመው አብሮ በመሰብሰብ የተለያዪ ስነ-ሥርዓቶች፣ የተመረጡ መጻህፍትን ማንበብ ወዘተ። በነዚህ ሁለቱ መሠረት ቃሉ ላይ ብንነጋገር ሰዎች የሰጡትን ምንም አይነት አሉታዊ ትርጉም አናገኝም።

የሥነ-ስርዓት(rituals) ንቀት

አንዱ የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች የሚታይባቸው ትልቅ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ስህተት የሥነ-ስርዓቶችን ታላቅ ቦታ አለመረዳት ነው። ለነዚህ ሰዎች ስርዓት ከሆነ ውጪያዊ ተግባር እንጂ ከእግዜር ጋር ያለን ግንኙነት ጋር የሚካተት አይደለም። ለምሳሌ በክርስትና ውስጥ ያሉት ሁለቱ ታላቅ ስርዓቶች የቅዱስ ጥምቀት እና ቅዱስ ቁርባን ሥነ-ስርዓቶች ናቸው። እነዚህን ዝምብሎ የሰው ውጪያዊ ስርዓት ፍጸማ ብሎ በማሰብ ከመጽሃፍ ቅዱስ ይርቃሉ። እግዜር በሥነ-ስርዓቶች ተጠቅሞ ጸጋና በረክትን ሊሰጥ እንደሚችል አልተገነዘቡም። ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት የሚጠብቅበት፣ የሚለመልምበት አንዱም መንገድ እነዚህ ስነ-ሥርዓቶች እንደሆኑ ፈጽሞ አለመገንዘብ። በቅዱስ ጥምቀት ወደ ክርስቶስ አካል ነው ምንጠመቀው፣ በቅዱስ እራቱ ደሞ ህይወት ከሚሰጠው የክርስቶስ ስጋና ደሞ እኮ ነው ምንካፈለው። እነዚህ ከክርስቶስ ጋር ህብረት ማረግ ካልሆኑ ምን ሊሆን ነው? ይህን ስንል ግን ሉተራዊያን አጥበቀው የሚያስተምሩት እነዚህ ሥነ-ስርዓቶችም ጭምር ጸጋና በረከተን የሚሰጡት በእምነት ከቀረብናቸው ነው እንጂ እንድሁ ስለተሳተፍንባቸው ብቻ አይደለም ብለው ያስተምራሉ።

ክርስትናን ከቤተክርስትያን የሚነጥል

ቅዱስ ቆጵርያኖስ እውቅ የተናገረው ነገር አለ፡ "ቤተ ክርስቲያንን እናቱ ያላደረገ፥ እግዚአብሔርን አባቱ ሊያደርገው አይችልም።" ይሄ ከሉተራዊያን የነገረ-ቤተክርስትያን እውቅ ሃረግ አለ፡ "Extra Ecclesiam nulla salus"። ይህም ከቤተክርስትያን ውጪ ድህነት የለም የሚል ሃረግ ነው። ይህን ሃረግ ሉተራዊያን ሲጠቀሙት ልክ ኦርቶዶክሳዊያን እንደሚጠቀሙት አይደለም የምንጠቀመው። ሰው በእምነት ብቻ ነው የሚድነው የሚል አቋም ስላለን ከአንድ የምትታይ ቤተክርስትያን ጋር ድህነትን አያይዘን እዚህ ቤተክርስትያን ውስጥ ካልገባህ አትድንም የሚል ምልከታ የለንም። ነገር ግን ይህ ሃረግ ትርጉሙ እውነተኛ አማኞች የሚገኙት በምትታየው ቤተክርስትያን ውስጥ ነው እንጂ ከእርሷ ውጪ አይደለም። ሰው ድህነትን የሚፈልግ ከሆነ በምትታየው ቤተክርስትያን ውስጥ ነው ይህን የሚያገኘው። ወንጌሉን ከተቀበለ በኋላ እስከመጨረሻ እንዲጸና የሚያስችለውን ጸጋ እግዜር በቤተክርስትያን በኩል ነው ሊሰጥ የወደደው። የዚህ ሃገር አቀንቃኞች ከቤተክርስትያን ውጪ ያለንን መንፈሳዊ ህይወት አስፈላጊነት በማጉላት ይታወቃሉ። ቤተክርስትያን ያለው አይደለም ዋናው፣ ዋናው በየቀኑ እቤት ያለን ከጌታ ጋር ያለን የግል ሰዓት ነው ይላሉ። ይሄ ፍጹም ጠኔኛ የሚመስል ንግግር ነው ምክንያቱም መጽሃፍ ቅዱስም የዕለት ተዕለት ኑሮዋችን እንደሆነ ይነግረናል። ነገር ግን ይሄ የሚስተው ነገር ሳያውቀው የቤተክርስትያንን ሚና ያደበዝዛል። ሰለ ግል ህይወት ፍጹም አስፈላጊነት ብቻ አውርቶ ስለ ቤተክርስትያን አለማውራት ወይም ደሞ ጭራሽ የቤተክርስትያንን ሚና ማጣጣል ያመጣው የሚታይ ውጤት ቤተክርስትያን የለሽ ክርስትያኖችን አፍርቷል። እኔ ቤተክርስትያኗ ማገኘው ነገር ጥሩ አይደለም፣ ለዚያ ከሄድኩ ራሱ 2 አመቴ፣ ግን እፅልያለው፣ መጽሃፍ ቅዱሴን አነባለው ያላሉ። አንዳንዶች ደሞ ጭራሽ እኔ መንፈሳዊ ነኝ እንጂ ሃይማኖተኛ አይደለሁም በማለት ሙሉበሙሉ ራሳቸውን ከቤተክርስትያን የለዪም አሉ። እንደው ከነዚህ ውጪም አማኞች የቤተክርስትያንን ሚና ባለመረዳት በሰንበት ዕለት ከቤተክርስትያን መቅረት እምብዛም እንደ ትልቅ ነገር ባለማየት ለወራት በተከታታይ ሊቀሩ ይችላሉ፣ ወይም ደሞ በ3 ወር አንዴ ሊሆን ይችላል ይሚታደሙት። ይሄ ፍጹም መጽሃፍ ቅዱሳዊ የቤተክርስትያን አረዳድ አይደለም። መጽሃፍ ቅዱስ በግልጽ አማኞች ሁሉ በምትታየው ቤተክርስትያን ውስጥ እንደሆኑ ያስነብባል፣ በቤተክርስትያን በኩልም እንደሆነ እስከ መጨረሻ ምንጸናበት ጸጋ እግዜር ሊሰጥ የወደደውም፣ ያለ ቃሉና ተቀደሱት ሚስጥራት ክርስትና የለም።

መደምደሚያ

ይሄ ሃረግ አማኞችን ለግለኝነት፣ የቤተክርስትያንን ሚና ወደ መናቅ፣ እና ከሁሉም በላይ ደሞ እግዜር በቃሉ መልካም ብሎ የጠራውን ቃል የራስ ትርጉም በመለጠፍ አማኞች ቃሉን በአሉታዊ መንገድ እንዲያዪ የሚያረግ አደገኛ ሃረግ እንደሆነ ለማሳየት ሞክርያለሁ። እባካችሁን ፅሎታችን የሃይማኖት መንፈስ ንቀል ከሚል ልክ እንደ ቅዱስ ያዕቆብ በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖትን በሰዎች ልብ ላይ አንግስ ይደግ።